አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴው ግድብ ላይ ያላትን አቋም ለማስረዳት ወደተለያዩ የዓለም ሀገራት ከፍተኛ የልኡካን ቡድኖችን በመላክ ላይ ትገኛለች።
በዚሁ መሰረት በኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የተመራ ከፍተኛ የአገራችን የልኡካን ቡድን በዛሬው እለት ኬንያ ናይሮቢ በመገኘት ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ያላትን ግልጽ አቋም ለፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አስረድቷል።
ሁለቱ መሪዎች ክህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ያደረጉትን ውይይት ተከትሎም የጋራ የአቋም መግለጫ ማውጣቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሚመራው የልኡካን ቡድን በቀጣይም በሌሎቹ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ተመሳሳይ ጉብኝት በማደረግ ለአባል ሀገራቱ መሪዎች የኢትዮጵያን አቋም እንደሚያስረዳ ይጠበቃል።
በተመሳሳይ በቀደሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የተመራው ከፍተኛ የኢትዮጵያ የልኡካን ቡድን ከዛሬ ጀምሮ በአውሮፓ በመገኘት ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ያላትን ግልጽ አቋም የሚያስረዳ ይሆናል።
ልኡኩ በቆይታውም ከአውሮፓ ህብረት ፕሬዚዳንት፣ ከፈረንሳይ እንዲሁም ከሌሎች የህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች ጋር በመገናኘት ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን አቋም ለማስረዳት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።
በቀጣይም ተመሳሳይ ከፍተኛ የኢትዮጵያ የልኡካን ቡድን በአሜሪካ እና በሌሎች ሀገሮች በመዘዋወር ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያላትን ግልጽ አቋም እንደሚያስረዳ ይጠበቃል።

