Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በማዕከላዊ ጎንደር 6 ህፃናትን በአሰቃቂ ሁኔታ የረሸነና የወረዳውን ሰላም ሲያውክ በነበረ ግለሰብ ላይ የፀጥታ አካላት እርምጃ ወሠዱ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጠገዴ ወረዳ ሰላምና ደኅንነት ጽ/ቤት 6 ህፃናትን በአሰቃቂ ሁኔታ የረሸነና የወረዳውን ማህበረሰብ ሰላም ሲያውክ በነበረ ግለሰብ ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

ሀብታሙ አዛናው በቅፅል ስሙ” ጭላት” የተባለው ግለሰብ በ2012 ዓ.ም ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን 6 ህፃናትን በአሰቃቂ ሁኔታ የረሸነ፣ ሰው በማገት ገንዘብ በመቀበል እንዲሁም ሰው የመግደልና መሰል ችግሮችን በመፍጠር በአካባቢው እየተዘዋወረ የማህበረሰቡን ሰላም ሲያውክ  እንደነበር ተገልጿል፡፡

በዚህም ሀምሌ 22 ቀን 2014 ዓ.ም  በጠገዴ ወረዳ  ማይ አጋም ቀበሌ ልዩ ስሙ ባውታ በተባለ ቦታ ላይ  የወረዳው የጸጥታ መዋቅር ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት በአካባቢው ሰው ለማገት ሰንሰለት ይዞ ሲንቀሳቀስ  እጅ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ እርምጃ መውሰዱን የወረዳው ሰላምና ደህንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ለምለሜ አጣናው  ተናግረዋል፡፡

ሃላፊው  የወረዳው የጸጥታ መዋቅር ላሳየው ቁርጠኝነትና የአካባቢው  ማህበረሰብ ወንጀለኛን በማጋለጥና ጥቆማ  በመስጠት ላሳየው ትብብር  ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ÷ ሰላምን ለማረጋገጥ  ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ከጠገዴ ወረዳ የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

Exit mobile version