አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በነሐሴ የሚኖረውን የተጠናከረና ተከታታይነት ያለው ከባድ ዝናብ ተከትሎ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ጎርፍና የወንዞች ሙላት እንዲሁም የመሬት መንሸራተት ሊኖር እንደሚችል የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡
በመሆኑም በየአካባቢው ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኢንስቲትዩቱ መክሯል፡፡
በመጪው ነሐሴ ÷ በሰሜን ምስራቅ፣ በሰሜን፣ በሰሜን ምዕራብ እና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች የተሻለ ጥንካሬ እንደሚኖራቸው የትንበያ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
በሚቀጥለው ወር÷ የምዕራብ፣ የምስራቅ እና የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ ጂማ፣ አዲስ አበባ ዙሪያ፣ አዲስ አበባ፣ ሁሉም የአማራ ክልል እና የትግራይ ዞኖች እንዲሁም የአፋር ክልል ዞኖች በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበና በአንዳንድ ቦታዎቻቸው ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ የኢንስቲትዩቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሁሉም አካባቢዎች፣ የሀድያ፣ የጉራጌ፣ የስልጤ፣ የወላይታ፣ ጌዲዮ ዞኖች እንዲሁም የሲዳማ ክልል እና የደቡብ ምዕራብ ክልል ዞኖች፣ ቄለም ወለጋ፣ ኢሉአባቦራ፣ ቡኖ በደሌ፣ አርሲ እና የምዕራብ አርሲ ዞኖች፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ድሬዳዋና ሐረሪ፣ ሁሉም የጋምቤላ ዞኖች፣ ሲቲ እና የፋፈን ዞኖች ከሚኖራቸው እርጥበት አዘል አየር ጋር ተያይዞ በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ የዝናብ መጠን ያገኛሉ፡፡
እንዲሁም የተቀሩት የሀገሪቱ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ከሚኖራቸው የደመና ሽፋን መጨመር በስተቀር በአብዛኛው ደረቅ ሆነው እንደሚቆዩ ትንበያዎች ማመላከታቸውን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!