አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዳያስፖራው ማህበረሰብ በሀገሪቱ ዘላቂ ጥቅም ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የበለጠ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ ኢድሪስ÷ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ለማጠናከር እና ራሷን ለማስተዋወቅ ዳያስፖራዉ የሀገሩ አምባሳደር እንደመሆኑ ጠንካራ ስራዎች እንደሚሰራ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ይህ መልከ -ብዙ ጥቅም ያለው የዳያስፖራው ተሳትፎ በሚፈለገው ደረጃ ያድግ ዘንድ ደግሞ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
ስለ ሀገር ለመምከር የሚረዱና በመንግስትና በዳያስፖራው መካከል ያሉ ግንኙነቶችን ለማበርታት የተጀመሩ ወደ ሀገር ቤት ጥሪዎችም አበረታች ውጤቶች እንደታዩባቸው የገለጹ ሲሆን÷ ይህም በቀጣይ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ አጽንኦት ለመስጠት ስለማገዙ አንስተዋል፡፡
በአሜሪካና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሚዲያውን በመጠቀም ስለ ሀገር ጉዳይ እውነታዎችን በማስረዳት የሚታወቀው ዑስታዝ ጀማል በሽር በበኩሉ÷ የዳያስፖራው ማህበረሰብ የጀመራቸውን ስራዎች ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግሯል፡፡
በተለይም አሁን ላይ ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር እና ማሳደግ የሚያስፈልግበት ወሳኝ ጊዜ እንደመሆኑ ስለ ሀገር መተባበር ይገባናል ብሏል ፡፡
ኑሯቸውን በአውሮፓ፣መካከለኛው ምሥራቅና ሌሎች አካባቢዎች ያደረጉ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ደግሞ በጦርነት የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ የሚደረገውን ተሳትፎ እና ሌሎች በጎ ስራዎችን ማበርታት እንዲሁም ለሀገር ሰላም በጋራ በመቆም ዳያስፖራው የድርሻውን ማበርከት እንዳለበት ነው የጠቁሙት፡፡
በጎ ስራዎች ጠንካራና ዘላቂ ሆነው ይቀጥሉ ዘንድም የመረጃ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ማድረግ እና ሀገርን በሁሉም መስክ ለመደገፍ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተቋማዊ መልክ እንዲኖራቸው ማስቻል ይገባል ሲሉም አመላክተዋል፡፡
በአወል አበራ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!