Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያና የቻይና የውጭ ጉዳይ አቻ ተቋማት ተባብሮ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ተቋም እና የቻይና ህዝብ የውጭ ጉዳይ ተቋም በጋራ ተባብሮ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ተስማሙ፡፡

የተቋማቱ ተወካዮች በሚሲዮኑ አስተባባሪነት የኦንላይን ውይይት አካሂደዋል፡፡

አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ፥ ቻይና እና ኢትዮጵያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸው፥ እ.ኤ.አ በ2017 ግንኙነታቸው ወደ ሁሉን-አቀፍ ስትራቴጂያዊ ትብብር ደረጃ ማደጉን ተናግረዋል።

አክለውም ባሳለፍነው ዓመት በሴኔጋል ርዕሰ መዲና ዳካር የተካሄደው 8ኛው የአፍሪካ ቻይና ትብብር ፎረም የሚኒስትሮች ኮንፈረንስ ካስቀመጣቸው ዘጠኝ ዋና ዋና የትብብር መስኮች መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አንደኛው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሁለቱ አቻ ተቋማት በተለይም በጋራ የምርምር ስራዎች፣ በመረጃ፣ ህትመትና ልምድ ልውውጥ እንዲሁም የጋራ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ተባብረው እንዲሰሩና ግንኙነታቸውን የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ኤክስኪውቲቭ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ አምባው ፥ ሁለቱ ተቋማት የካበተ ልምድ ያላቸው ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትልቅ አቅም አላቸው ብለዋል፡፡

አክለውም ከቻይናው አቻ ተቋም ጋር አምባሳደሩ በጠቀሷቸው የትብብር መስኮች ዙሪያ ተባብሮ ለመስራት ፅኑ ፍላጎት ያላቸውና ለዚህም ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የቻይና ውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ፕሬዚዳንት አምባሳደር ሊ ዢ ፥ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ትልቅ ሥፍራ የምትሰጥ መሆኑንና ቻይና ከአፍሪካ ጋር ለምታደርገው ትብብር ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና ያላት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ተቋማቸው በቀረቡት የትብብር መስኮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

አክለውም ፥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተባቸው የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሌሎች የዓለም ሀገራት አየር መንገዶች በተለየ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ ሳያቋርጥ ቻይናንና አፍሪካን በማገናኘት የተለያዩ የህክምና መርጃ መሳሪያዎች ለመላው አፍሪካውያን ተደራሽ እንዲሆኑ በማስቻሉም አመስግነዋል፡፡

አየር መንገዱ በቻይና መንግስት ሙሉ እምነት የሚጣልበት መሆኑን መግለጻቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version