Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሚኒስቴሩ በታክስ ኦዲት 52 ነጥብ 34 ቢሊየን ብር ከምዝበራ ማዳኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር በ2014 በጀት ዓመት  በታክስ ኦዲት 52 ነጥብ 34 ቢሊየን ብር ከምዝበራ ማዳን መቻሉን አስታወቀ፡፡

በ2014 በጀት ዓመት በተሠራው የታክስ ኦዲት አላግባብ ለመጠቀም ወይም ግብርን ለመሰወርና ለማጭበርበር ታስቦ የተሠራውን ህዝብና ሀገርን የሚጐዳ ተግባር በተቋሙ ኦዲተሮች መልካም ስራ ለማዳን መቻሉ ተመላክቷል፡፡

በዚህም 2 ሺህ 156 ግብር ከፋዮች 51 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ተገቢነት የሌለው ኪሣራ አቅርበው ኦዲት ሲደረግ ትክክል አለመሆኑ መረጋገጡ ነው የተገለጸው፡፡

በተጨማሪም 320 ግብር ከፋዮች 0 ነጥብ 45 ቢሊየን ብር ተገቢነት የሌለው ቅድመ ግብር ተመላሽ ጠይቀው ኦዲት ሲደረግ አላግባብ ለመጠቀም የተሠራ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

ከዚህ ባለፈም  588 ግብር ከፋዮች 0 ነጥብ 74 ቢሊየን ብር ተገቢነት የሌለው የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመላሽ ጠይቀው በታክስ ኦዲተሮች ሲረጋገጥ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጦ እንዳይወሰድ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 3 ሺህ 299 ግብር ከፋዮች በሰሩትና ባተረፉት ልክ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ታክስ መክፈል ሲገባቸው ከላይ በተጠቀሱት ተገቢነት በሌለውና ሀገርና ህዝብን በሚጐዳ መንገድ ታክስ በመሰወርና በማጭበርበር ራሳቸውን ለመጥቀም የሠሩትን መጥፎ ተግባር የተቋማችን የታክስ ኦዲተሮች 52 ነጥብ 34 ቢሊየን ብር የሀገርን ሀብት ማዳን መቻሉ ተገልጿል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው ይህን መልካም ተግባርና ሀገራዊ ኃላፊነት ለተወጡ ኦዲተሮች ምስጋና ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ታክስ በመሰወርና በማጭበርበር ድርጊት ውስጥ ለመግባት የሚሞክሩ  ደንበኞችም ከዚህ መጥፎ ድርጊት በመውጣት ምስጉንና የታክስና የቀረጥን ህግና ስርዓትን አክብረው ለህዝባቸውና ለሀገራቸው የበኩላቸውን አስተዋጾኦ እያደረጉ ያሉ ታማኝ ግብር ከፋዮችን አርዓያ እንዲከተሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

Exit mobile version