አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የቻይናው የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል (ሲ ዲ ሲ) በጋራ ተባብሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
ተቋማቱ ባካሄዱት የኦንላይን ስብሰባ÷ የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ስርዓታቸው የተሻለ እንዲሆን ለማድረግና ትብብራቸውን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ስምምነቱ በመጪዎቹ ዓመታት በሁለቱ ተቋማት መካከል የሚደረጉ ትብብሮችን የሚያጠናክርና ግንኙነታቸውንም ይበልጥ የሚያሳልጥ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በሁለቱ ተቋማት መካከል የተጀመረው ይህ ግንኙነት በአፍሪካ ቻይና የትብብር ፎረም ማዕቀፍ አፍሪካና ቻይና በህክምናው ዘርፍ ለሚያደርጉት ትብብር ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር መሳይ ኃይሉ÷ ትብብሩ ፍሬያማ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሠራ መናገራቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡
የቻይና የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል ዳይሬክተር ጄኔራል ፕሮፌሰር ሺን ሆንግቢንግ በበኩላቸው÷ ለትብብሩ ውጤታማነት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱ እንዲፈረም በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲን ጨምሮ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

