Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አባላት ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አመራሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አባላት ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው በቀጣይ በመዲናዋ ስለሚያከናወኑት ተግባራት እና መንግስት እንደ አንድ ባለድርሻ አካል በሚጠበቅበት ሚና ላይ መነጋገራቸውም ነው የተገለጸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ÷ በሚደረገው ሀገራዊ ውይይት የከተማው ሕዝብ በአግባቡ ተወክሎ እንዲወያይ እንዲሁም ከዝቅተኛ ገቢ እስከ ባለሐብት ድረስ ያለ እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል በአግባቡ እንዲወከል እንደ ከተማ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ላይ ተሥፋ ብቻ ሳይሆን ዕምነትም ጭምር አለን ያሉት ከንቲባ አዳነች የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ በሆነ መንገድ ካወያዩት ወደ መግባባት እና ወደ አንድነት የማይመጣበት ምንም ምክንያት የለምም ብለዋል፡፡

የምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ዓርዓያ ÷ ከዕርቀ ሠላም ኮሚሽኑ በየተለየ የምክክር ኮሚሽኑ በአዋጅ የተቋቋመ እና አጀንዳዎች በዋናነት ከኅብረተሰቡ ወስዶ ውይይት እንዲደረግባቸው በማመቻቸት የጋራ መግባባት ማምጣት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሂሩት ገብረ-ሥላሴ ሀገራዊ ምክክሩ እስከ ዛሬ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ የሐሳብ አለመግባባቶችን እና የዕሴቶች መሸርሸርን ይፈታል ብለዋል፡፡

በከተማው የሚገኙ አስተዳደራዊ ተቋማት የኮሚሽኑን ተልእኮ ለማሳካት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያለምንም ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድ እንዲያከናውኑም በከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አቅጣጫ መቀመጡን ከከንቲባ ጽኅፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version