አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ስታራምድ የቆየችውን የ”አንድ ቻይና” ፖሊሲ አቋሟን እንዳጸናች መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ገለጹ።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነትን የሚያጠናክር ውጤታማ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ማድረጓንም ተናግረዋል።
አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚከሰቱ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች እንደሚያሳስቧት ገልጸው ሰሞኑን በቻይና-ታይዋን ጉዳይ የተከሰተውን ውጥረትም በትኩረት እየተከታተለች መሆኑን ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ የ“አንድ ቻይና” ፖሊሲ አቋም ዛሬ የተጀመረ አይደለም ያሉት አምባሳደር መለስ፥ ከቻይና ጋር በነበረን ግንኙነት ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስታት አፅንተው የያዙት አቋም ነው ብለዋል።
አሁንም ኢትዮጵያ ለ“አንድ ቻይና” ፖሊሲ ፅኑ አቋም እንዳላት ጠቁመው፥ ፖሊሲውን ኢትዮጵያ አባል የሆነችባቸው የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረትም የሚያራምዱት አቋም መሆኑን አክለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረትና ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኞች ጋር መወያየታቸውን የጠቀሱት አምባሳደር መለስ፥ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ፅኑ አቋም ደግመው ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።
መልዕክተኞቹም የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ እንደገለጹም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነትን የሚያጠናክር ውጤታማ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አንስተዋል።
በሌላ በኩል በተለያየ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የውጭ ሀገር ዜጎችን የመኖሪያ ፈቃድ ለመስጠትና ለኢሚግሬሽን አሰራር አመቺነት ሲካሄድ የቆየው የመጀመሪያው ዙር ምዝገባ ትናንት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።
በዚህም 66 ሺህ ያህል የውጭ ዜጎች ምዝገባ መከናወኑን ጠቁመው፥ ያልተመዘገቡ ዜጎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂ እንደማይሆን ገልጸዋል።
አምባሳደር መለስ ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ለጎረቤቶቿ ቀዳሚ ሥፍራ እንደምትሰጥ በማንሳት ከጎረቤቶቿ ጋር ያላት ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሁንም አበክራ እየሰራች ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

