Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኤምባሲው በአራት ወራት የ542 ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን ሕይወት መታደጉን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለፉት አራት ወራት ብቻ የ542 ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን ሕይወት መታደጉን ገለጸ፡፡
እጅግ በጣም አደገኛ ከሆነው የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰዋራ መንገዶች ተርፈው፣ የከፋ አደጋ ወደሚደርስበት የጂቡቲ የባህር ላይ ጉዞ የሚያደርጉ ዜጎችን ሕይወት ለማትረፍ ከጂቡቲ የባህር ዳርቻ ጥበቃ ኃይል ጋር በቅርበት በመሥራቱ፥ ባላለፉት 4 ወራት ብቻ የ542 ፍልሰተኞችን ሕይወት ማትረፍ መቻሉ ተገልጿል፡፡
በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሐምሌ 22 ቀን 2014 ዓ.ም በጂቡቲ በኦቦክ ክልላዊ መስተዳደር ራስብር በተባለ አካባቢ 55 ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን አሳፍራ ወደ የመን የምትንቀሳቀ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ጀልባ በቁጥጥር ስር በማዋል አላስፈላጊ የሕይወት መጥፋት እንዳይከሰት መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች ሕገወጥ ጀልባዎችን በመጠቀም ከየመን ወደ ጅቡቲ እንዲሁም በተቃራኒ አቅጣጫ በሚያደርጉት ጉዞ በጂቡቲ የባህር ዳርቻዎች ተደጋጋሚ የጀልባ መገልበጥ አደጋዎች ደርሰው ዜጎችን ለሞት መዳረጋቸው ተጠቅሷል፡፡
በተሳሳተ መረጃ፣ በሕገ ወጥ ደላሎች ተታለው የሌሎች አገራት ድንበርን በማቋረጥ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ የሚወጡ ዜጎች ይሄንን መገንዘብ እና ወደዚህ ወጥመድ ላለመግባት መጠንቀቅ እንዳለባቸው አጽንዖት ተሰጥቷል፡፡
ኤምባሲው የጂቡቲ የባህር ዳርቻ ጥበቃ ኃይል እና ብሔራዊ ባህር ኃይል ፍልኃኞችን ለመታደግ ለሚያደርገው ዘመቻ አመስግኗል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version