Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመርሀቤቴ ወረዳ በጎርፍ አደጋ 4 የአንድ ቤተሰብ አባላት ሕይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ሸዋ ዞን መርሀቤቴ ወረዳ በጎርፍ አደጋ 4 የአንድ ቤተሰብ አባላት ሕይወት ማለፉን የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር የሺዓለም እንደሻው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ አደጋው ትናንት ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ነው የደረሰው፡፡

የግብርና ሥራን ለማከናወን ሦስት ልጆቹንና አንድ የልጅ ልጁን ይዞ ከመርሀቤቴ ወደ ሚዳ ወረሞ ወረዳ የተጓዘው አባወራ “ወንጭት” ወንዝን ሲያቁርጡ በደራሽ ጎርፍ ተወስደዋል።

በዚህ አደጋ የአባትን ሕይወት ማትረፍ ሲቻል ቀሪዎቹ የቤተሰብ አባላት ሕይወታቸው አልፏል።

በአደጋው ሕይወታቸው ካለፉት መካከል የ15 ዓመት ዕድሜ ያላትን ታዳጊ አስከሬን ማግኘት ሲቻል÷ የሦስቱ አስከሬን በፍለጋ ላይ መሆኑንም ፖሊስ ገልጿል።

ወቅቱ የጎርፍ አደጋ የሚከሰትበት በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በአላዩ ገረመው

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version