አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 2 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከምዕራብ አርሲ ዞን ፖሊስና ከሌሎች ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት 122 ኩንታል አደገኛ ዕፅ ይዞ ማስወገዱን ገለጸ።
የሻሽመኔ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሽመልስ ቀናው በወረዳው ውስጥ አደገኛ ዕፅ ለመቆጣጠር ተከታታይ የፓትሮል ቅኝትና ከፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማውጣት ቤት ለቤት በተደረገው ድንገተኛ ብርበራና ፍተሻ አደንዛዥ ዕፁንና ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደተቻለ ተናግረዋል።
ከሌላው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ እንደሆነ የገለጹት ኮማንደሩ፥ ዕጹ የትውልዱን አእምሮ አደንዝዞ ለወንጀል ድርጊት ስለሚገፋፋ በሀገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳትና አስከፊነት በመገንዘብ አደንዛዥ ዕፅ ያበቅላሉ ተብለው በሚጠረጠሩ ቀበሌዎች ላይ ለሕብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በወረዳው አደገኛ ዕፅን በዘላቂነት ለማጥፋት የቀበሌ አመራሮችን እና የአካባቢውን ማሕበረሰብ በማስተባበር ከግብርና ባለሙያዎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በአካባቢው እንዳይበቅል በትኩረት እየተሰራበት መሆኑንም አመላክተዋል።
ከዚህ ባለፈም በመሬቱ ላይ ዕፁን የሚያበቅል አርሶ አደር ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድበትና መሬቱም ሳይቀር እንደሚወረስ ገልጸዋል፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አምስት ተጠርጣሪዎች ተይዘው ሕግ ፊት ቀርበው ከሦስት ዓመት እስከ ስድስት ዓመት የፍርድ ውሳኔ እንደተሰጠባቸውመናገራቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኮማንደር ሽመልስ አደገኛ ዕጹን የሚያመርቱ እና የሚያዘዋውሩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀው÷ ይህን ተላልፈው በሚገኙ ሰዎች ላይ የተጠናከረ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝበዋል።

