አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር በ2015 ዓ/ም በጀት ዓመት መጀመሪያ በሆነው ሐምሌ ወር ብቻ ከ28 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ በሐምሌ ወር ሊሰበስብ ካቀደው 29 ቢሊየን 521 ሚሊየን 905 ሺ 411 ብር ውስጥ 28 ቢሊየን 766 ሚሊየን 473 ሺ 727 ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 97 ነጥብ 44 በመቶ ማሳካት መቻሉን የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው ገልፀዋል።
አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር የብር 6 ቢሊየን 477 ሚሊየን 742 ሺህ 380 ወይም የ29 ነጥብ 06 በመቶ እድገት እንዳለው ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የተሰበሰበው ገቢ ምንጭ ከአገር ውስጥ ታክስ 16 ቢሊየን 88 ሚሊየን 891ሺህ 812 ብር የሚሸፍን ሲሆን ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ ደግሞ 12 ቢሊየን 677 ሚሊየን 581 ሺህ 915 ብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ላቀ አያሌው ለዚህ ስራ መሳካት የየድርሻቸውን ለተወጡ አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የዚህ ወር አፈፃፀም የበጀት ዓመቱ የተጀመረበት እንጂ የተጋመሰበት ባለመሆኑ ሁላችንም የጀመርነውን በቅንጅት የመስራት ተግባር አጠናክረን ልንቀጥል ይገባልም ነው ያሉት፡፡

