አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ከ104 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የመስኖና የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተመረቁ።
የክልሉ ውሃ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ እንደገለጹት÷ በክልሉ በዚህ አመት 18 የመስኖ ተቋማት ግንባታ በማጠናቀቅ 1ሺህ 800 ሄክታር መሬት ለማልማት እየተሰራ ነው።
ሀላፊው ገለጻ የህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተደረገ ጥረት 305 ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለምረቃ ማብቃት ተችሏል ብለዋል።
በጋሞ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ከ104 ሚሊየን ብር በላይ 10 የመስኖና የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉንም ጠቁመዋል።
አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም እያካሔደ ያለውን የመስኖ ተጠቃሚነት ውጤታማ ለማድረግ ዘመናዊ የመስኖ ተቋማትን ለማስፋፋት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
የደቡብ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማት እና አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ወ/ጊዮርጊስ ÷ በክልሉ በ2014 በጀት አመት ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ 46 የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ሲካሄድ መቆየቱን አብራርተዋል።
ከነዚህ ውስጥ 18 ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እንደተቻለ መናገራቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡