Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሠመራ ከተማ ጎርፍ ባስከተለው አደጋ የ3 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ ጎርፍ ባስከተለው አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ቢልኢ አህመድ እንደገለጹት÷ አደጋው የደረሰው ትናንት ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ የሎግያ ወንዝ ከመጠን በላይ ሞልቶ አካባቢውን በማጥለቅለቁ ነው።

ከሌላ አካባቢ የጣለው ዝናብ ወንዙ ይዞት የሚመጣውን ውሃ እየጨመረ በመምጣቱ ግድቡን ተሻግሮ ወደ ጂቡቲ በሚወስደው አስፋልት መንገድን አቋርጦ ሲፈስ ማደሩን ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ በመንገዱ ላይ የተጥለቀለቀውን የጎርፉን ውሃ በእግራቸው ለማቋረጥ የሞከሩ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ኮማንደር ቢልኢ ተናግረዋል፡፡

ሌሎች ተጨማሪ ሰዎች በውሃው ተወስደዋል የሚል ጥርጣሬ በመኖሩ የጸጥታ ሃይሉና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች የማፈላለግ ስራ እያከናወኑ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተጨማሪም መንገዱን ሲሻገሩ በተወሰዱ ሁለት ተሽከርካሪዎች ላይ የነበሩ ስምንት ሰዎች በአደጋ ጊዜ ሰራተኞችና በህብረተሰቡ ርብርብ ህይወታቸውን ማትረፍ መቻሉን አስታውቀዋል።

 

Exit mobile version