Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሶለል፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፥ የእንግጫ ነቀላና ከሴ አጨዳ በድምቀት እንደሚከበሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሁለት ዓመታት በኋላ ሶለል፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ እና የእንግጫ ነቀላና ከሴ አጨዳ በተፈጥሯዊ መገኛቸው በድምቀት እንደሚከበሩ የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮንን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ መልክ ያላቸው ሶለል፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ እና የእንግጫ ነቀላና ከሴ አጨዳ ዘንድሮ በክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት ይከበራሉ፡፡
በዚህም ከነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የቡሄ በዓል እንደሚከበር ጠቁመው÷ ይህም “ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር” በሚል መሪ ሐሳብ ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ፣ በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት አደረጃጀቶች እና የአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባባር በፓናል ውይይት እና በአደባባይ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሻደይ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን ከነሐሴ 14 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚከበር ገልጸው÷ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በአደባባይ ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም ይከበራል ብለዋል፡፡
ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዓ.ም የመስቀለ ክርስቶስ ፍልፍል ውቅር ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ በሰቆጣ ከተማና አካባቢው የሚገኙ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርሶች እንደሚጎበኙ እና በዕለቱ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ አመላክተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም አሸንድዬ በላሊበላ÷ ሶለል ደግሞ በቆቦ ከተማ ከነሐሴ 16 እስከ 17 ቀን 2014 ዓ.ም በድምቀት እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡
ሰሜን ወሎ አካባቢ ያሉትን በዓላት በተመለከተ በክልል ደረጃ በወልዲያ ከተማ ከነሐሴ 19 እስከ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ይካሄዳል ነው ያሉት፡፡
በነሐሴ መጨረሻ ላይ ደግሞ÷ የእንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ በደብረ ማርቆስ ከተማ እንደሚከበር አመላክተዋል።
ከሁለት ዓመት በላይ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት በዓላቱ ሳይከበሩ መቆየታቸውን አስታውሰው÷ በዓላቱ በተፈጥሯዊ መገኛቸው እንዲከበሩ ሰፊ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል፡፡
በዚህም የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች አካባቢውን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ መልክ ያላቸው በዓላቱ በተፈጥሯዊ መገኛቸው እንዲከበሩ መደረጉ የአካባቢውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ያለመ በመሆኑ የተለየ ያደርገዋልም ነው ያሉት።
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version