አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 6፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የመቄዶኒያ የአረጋውያን እና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የገቢ ማሰባሰቢያ እና የምስጋና መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ሚሊኒዬም አዳራሽ ተካሄደ።
በመርሃ ግብሩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞች እና አርቲስቶችን ጨምሮ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች ታድመዋል።
የሚሰበሰበው ገቢ ማዕከሉ በአዲስ አበባ ከተማ በ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር እያስገነባ ላለው የአረጋውያን ማረፊያ ሆስፒታል የሚውል መሆኑ ተገልጿል።
በመርሃ ግብሩ የተለያዩ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በተጨማሪም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ 8161 አጭር የጽህፍ መልዕክትን በመጠቀም ተከናውኗል።
ማዕከሉ ሲጠናቀቅ ከአረጋውያን ማቆያ በተጨማሪ 120 አልጋ የሚይዝ ሆስፒታል እና የ120 መኪና ማቆሚያ ቦታ የሚኖረው ሲሆን ፥በአሁኑ ወቅት የግንባታ ሂደቱ 20 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።
መቄዶኒያ የአረጋዊያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ከዓመታት በፊት የተቋቋመ ሲሆን፥ ከ2 ሺህ በላይ ለሆኑ ራሳቸውን ችለው መመገብ፣ መፀዳዳት እና መንቀሳቀስ የማይችሉ አረጋዊያን እና የአዕምሮ ህሙማን ከየጐዳናው በማንሳት ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ማዕከሉ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና ሌሎች ክልሎች ከመንግስት ባገኘው ቦታ ቅርንጫፎችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑ ተጠቁሟል።
በዛሬው የገቢ ማሰባሰቢያ ስነ ስርዓት 80 ሚሊየን ብር ተሰብስቧል።

