Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ እና የቻይናው ዋይ ቲ ኦ ኩባንያ በጋራ ለመስራት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ እና የቻይናው ዋይ ቲ ኦ ኩባንያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
 
ስምምነቱን የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እና የቻይናው ዋይ ቲ ኦ ኩባንያ የአፍሪካ ዳይሬክተር ሊዩ ሁአጂን ናቸው የተፈራረሙት፡፡
 
ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ እና የቻይናው የግብርና ማሽኖች አምራች ኩባንያ ዋይ ቲ ኦ በጋራ ኮምባይነር፣ ትራክተር እና የትራክተር ተቀፅላዎችን አንድ ላይ ለማምረት እንዲሁም ለመገጣጠም ያለመ የትብብር ስምምነት ነው የተፈራረሙት።
 
ስምምነቱ ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ እና ዋይ ቲ ኦ ኩባንያ በትብብር በአፍሪካ ግዙፍ የተባለ የትራክተር ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት እንደሚያስችላቸው ተመላክቷል፡፡
 
በትብብር ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በቀጣይ በሶላር እና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ትራክተሮችን ለማምረት እንደሚሰሩ ተጠቁሟል፡፡
 
የሚመረቱት ትራክተሮችም ለአገር ውስጥ ብሎም ለአፍሪካና ለዓለም አገራት ጥቅም ላይ የሚውሉ መሆኑ ነው የተገለጸው።
 
በስምምነቱ መሰረት ትልቅና ዘመናዊ የተባለ የትራክተር መገጣጠሚያ ፋብሪካ የሚገነባ ሲሆን÷ በዓመትም 10 ሺህ ትራክተሮች መገጣጠም ያስችላል ተብሏል።
 
ከዚህ ቀደም በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ አማካይነት ይገጣጠሙ የነበሩ ትራክተሮችን ወደ ማምረቱ ደረጃ ለመድረስ የትብብር ስምምነት መደረጉ የጎላ ጥቅም እንዳለውም ተገልጿል።
 
በቅድስት ተስፋዬ
 
 
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version