Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የሥነ ምግባር ግድፈት ፈጽመዋል በተባሉ ዳኞች ላይ እርምጃ ወሰደ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የሥነ ምግባር ግድፈት ፈጽመዋል በተባሉ ሁለት ዳኞች ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ መውሰዱን ገለጸ።
የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ዛሬ ባከሄደው መደበኛ ስብሰባ÷ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛና የጉባዔ አባል የሆኑትን ዳኛ በረከት ሰይፉን በጉባዔው ሥር የተደራጀውን የጥቆማ ተቀባይ ክፍል እንዲመሩ በኃላፊነት መድቧል።
በሌላ በኩል የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ፋንታሁን ደለለው ወ/ሮ ሳጅዳህ ዘካሪያስ ከተባሉ አመልካች 100 ሺህ ብር በመቀበልና በአካል ከባለ ጉዳይ ጋር በመገናኘት ስለያዙት ጉዳይ በመወያየት የሐቀኝነትና የገለልተኝነት መርህ ተነጻጻሪ ግዴታዎችን በመተላለፍ ከባድ የሥነ-ምግባር ደንብ ጥሰት መፈጸማቸው በማስረጃ በመረጋገጡ ከዳኝነት ሥራቸው እንዲሰናበቱ ውሳኔ ተላልፏል።
ከዳኝነት ኃላፊነታቸው ሊሰናበቱ ይገባል ሲል በዳኞች የሥነ ምግባርና የዲሲፕሊን ክስ ሥነ-ስርዓት ደንብ ቁጥር 3/2014 አንቀጽ 34(3) መሰረት ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
ውሳኔው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሲጸድቅ ተግባራዊ እንደሚደረግ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መዓዛ አሸናፊ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም ጉባዔው የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ ዮናታን አበበ ላይ የቀረበውን በተመለከተ የቀረቡለትን የሰነድ እና የመዝገብ ማስረጃ ተመልክቶ ዳኛው ተደራራቢ የሥነ ሥርዓት ሕግ ጥሰት መፈፀማቸው በመረጋገጡ በአምስት ወር የደሞወዝ መቀጮ እንዲቀጡ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version