Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመተከል ዞን ወደ ማዕከል ለተመለሱ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን ከጫካ ወደ ማዕከል ለተመለሱ ዜጎች የተጠናከረ ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ድጋፍ ሰጪ ግብረ ሃይሉ ገለፀ፡፡

በዞኑ በዳንጉር ወረዳ እየተካሄደ ያለውን ህግ የማስከበር ተግባር ተከትሎ ከሰባት ቀበሌዎች ተፈናቅለው በጸረ ሰላም ሃይሎች ተጽዕኖ ጫካ ውስጥ የነበሩ ከ10 ሺህ 200 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተመልሰው በአይሲካ ማዕከል ተጠልለው ይገኛሉ።

በዞኑ ድጋፉን ለማጠናከር የተዋቀረው ግብረ ሃይል እና የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በመቀናጀት ለተፈናቃዮች አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል እየሰሩ መሆኑን የመተከል ዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ሃላፊ እና የግብረ ሃይሉ አስተባባሪ አቶ ታከለ ዋናየ ተናግረዋል።

የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው መደበኛ ስራቸውን እስከሚጀምሩ ድረስ የሰብዓዊ ድጋፉን ከማስቀጠል ባለፈ የጤና እና የውሃ ተቋማት አገልግሎቶችን በማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ሃላፊው አስታውቀዋል።

የዳንጉር ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሃብታሙ ባማኑ በበኩላቸው ÷በአንድ ማዕከል ተጠልለው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በጊዜያዊነት ፈጣንና ተደራሽ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህን ዜጎች ወደ ቀያቸው በመመለስ መደበኛ ኑሯቸውን እንዲኖሩ ወረዳው በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ለዜጎች ፈጣን የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ዩኒሴፍ፣ ፕላን ኢንተርናሽናል፣ ሚስሚዶ፣ አኒ እና ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ከመተከል ዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version