Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ “ትልቅ” የተባለለት ወታደራዊ ልምምድ ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ከዓመታት በኋላ ‘’ትልቅ’’ የተባለ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ እያካሄዱ መሆኑ ተሰማ፡፡

ሀገራቱ የጀመሩት ወታደራዊ ልምምድ ሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ ሙከራ ለማድረግ ከአጋሮቿ ጋር ዝግጁነቷን ለማጠናከር እየጣረች ባለበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡

”ኡልቺ የነጻነት ጋሻ” ተብሎ የተሰየመውና በፈረንጆቹ መስከረም 1 የሚጠናቀቀው ዓመታዊ የበጋ ልምምድ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችን “መደበኛ” ለማድረግና ከሰሜን ኮሪያ ሊቃጣ የሚችልን ጥቃት ለመከላከል ቃል ከገቡ በኋላ የመጣ ነው።

ደቡብ ኮሪያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግስትን ዝግጁነት ለማሳደግ የተነደፈ ነው የተባለለትን የአራት ቀናት የኡልቺ ሲቪል መከላከያ ልምምዶችን ትናንት በተናጠል ጀምራለች።

ወታደራዊና የሲቪል ልምምዶች በፋብሪካዎችና በአቅርቦት ሰንሰለቶች ላይ ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶችን እና የጦርነት ሁኔታዎችን ለመመከት የሀገሪቱን ዝግጁነት ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ሬውተርስ በዘገባው አመላክቷል።

ፕሬዚዳንት ዮን በኮሪያ ልሳነ ምድር ሰላም ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ደቡብ ኮሪያ ባላት ወታደራዊ አቋም ላይ እንደሚገነባ ለካቢኔ አባላቶቻቸው ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።

አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ልምምዶችን ለማድረግ የመጀመሪያ ደረጃ ስልጠና ከጀመሩ በኋላ ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ሳምንት ሁለት የክሩዝ ሚሳኤሎችን ከምዕራብ ጠረፍ ማስወንጨፏ ተገልጿል።

ሰሜን ኮሪያ በዚህ ዓመት በፍጥነት የሚሳኤል ሙከራዎችን ያደረገች ሲሆን ፥ ሰባተኛውን የኒውክሌር ሙከራዋን በማንኛውም ጊዜ ለማካሄድ ዝግጁ መሆኗን የሴኡል ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ደቡብ ኮሪያ ከጎረቤት ሰሜን ኮሪያ በኩል አለብኝ ለምትለው የሚሳኤል ጥቃት ስጋት የጥቃት ስጋቶችን ከመለየት ጀምሮ ወታደራዊ አቅሟን ለማሳደግ እንደምትሰራ አጽንኦት ሰጥታለች።

አሜሪካ ፣ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን በሃዋይ የባህር ዳርቻ የባለስቲክ ሚሳኤል የመከላከያ ልምምድ በቅርቡ ማድረጋቸው ይታወሳል ፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version