Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሀገር ልታጣ የነበረውን 50 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ማዳን ተችሏል – ጉምሩክ ኮሚሽን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2014 በጀት ዓመት ሀገር ልታጣ የነበረውን 50 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ማዳን መቻሉን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ የገቢዎች ሚኒስሯ ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ እና የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2015 በጀት ዓመት እቅድ ላይ እየተወያየ ነው፡፡

በመድረኩ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ÷ ኮሚሽኑ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በመንግስት የተሰጠውን ተልእኮ በብቃት የተወጣበት እንደነበር ገልጸው ያከናወናቸው ተግባራትም የሀገርን ኢኮኖሚ ያሳደጉ እና የህዝብን ደህነት ያስጠበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በሕገ ወጥ ንግድ ማጨበርበር እና ኮንትሮባንድ መከላከል ዙሪያ የውስጥ አቅም፣ የህብረተሰብ እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎን በማጠናከር እንዲሁም የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር፥ ሀገር ልታጣው የነበረውን 50 ነጥብ 4 ቢሊየን በላይ ማዳን መቻሉን ኮሚሽነሩ መግለፃቸውን ከጉምሩክ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ በ2014 በጀት ዓመት 5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎችና ህገ-ወጥ ገንዘብ መያዙ ተገልጿል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከተያዘው 5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃዎች ውስጥ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የሚገመተው የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች ሲሆን ÷ 836 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመተው ደግሞ የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች መሆኑ ተገልጿል፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት 154 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 140 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወይም የዕቅዱን 90 ነጥብ 7 በመቶ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸው፥ ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ28 ነጥብ 4 ቢሊየን ወይም የ24 በመቶ ብልጫ ማሳየቱንም ኮሚሽነር ደበሌ አውስተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version