አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በ2014 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 9 ሚሊየን ቶን የደረቅ ጭነት አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ÷ ተቋሙ በ2014 የበጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀምን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በበጀት ዓመቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትና ሌሎች ምክንያቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የንግድ መዛባት ማስከተላቸውን ጠቁመዋል።
በተለይም በአፈር ማዳበሪያ፣ በብረት፣ በነዳጅ፣ በስንዴ፣ በበቆሎ፣ በሱፍ ዘይት እና በሌሎች የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ የንግድ መዛባትና መስተጓጎል መከሰቱን አስታውሰዋል።
በዚህም ውስጥ ሆኖ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በሺፒንግ፣ በወደብና ሌሎች መሰል አገልግሎቶች በበጀት ዓመቱ 7 ነጥብ 9 ሚሊየን ቶን የደረቅ ጭነት አገልግሎት እንደሰጠ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የጭነት አገልግሎቱ በዋናነት በጂቡቲ ወደብ የተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው የድርጅቱ ዕቅድ አፈጻጸምም 92 በመቶ መሳካቱንም አመላክተዋል።

