አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለላሊበላና አካባቢው እየተገነቡ ከሚገኙት ከወልዲያ ወይም ከጋሸና ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ማገናኘት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
የአሸንድዬ በዓልን ምክንያት በማድረግ በላሊበላ ከተማ በተካሄደው ሕዝባዊ ውይይት ላይ÷ ነዋሪዎቹ ከኤሌክትሪክ፣ ከማህበራዊ አገልግሎትና ከቱሪዝም ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች አቀርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ከኤሌክትሪክ ጋር በተያያዘ ለቀረቡ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ÷ የዋግ ኽምራ ዞንና የላስታ ላሊበላ ከተማና አካባቢው ችግር የመነጨው አካባቢው በህወሓት ቁጥጥር ስር ካለው የአላማጣ ማከፋፈያ ጣቢያ ኤሌክትሪክ ያገኝ የነበረ በመሆኑና ወደተጠቀሱት አካባቢዎች ኃይል መልሶ ማገናኘት ባለመቻሉ ነው ብለዋል።
ይሁንና ከአላማጣ ኃይል ማገናኘት እስከሚቻል ድረስ አዲስ እየተገነባ ካለው ከወልዲያ ወይም ከጋሸና ማከፋፈያ ጣቢያ ለላሊበላና አካባቢው ኃይል ማገናኘት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየተሠራ ነው ማለታቸውን የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመላክታል፡፡
እየተሠሩ ያሉት ሥራዎች ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በቅርበትና በቅንጅት መሠራት ያለበት በመሆኑ ተገቢው ዝግጅት እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!