Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የባህር ኃይልን ለማዘመን የሚሠጡ ስልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ባህር ኃይል ለማዘመን ከሀገር ውጭ እና በሀገር ውስጥ የሚሠጡ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ በብላቴ የኮማንዶ እና የአየር ወለድ ኃይል ማሠልጠኛ ማዕከል ተገኝተው የማሪን ኮማንዶ የሚሠለጥኑ የባህር ኃይል አባላትን ጎብኝተዋል።

ዋና አዛዡ የስልጠና ሂደቱን ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ እንደተናገሩት÷ የማሪን ኮማንዶ ሠልጣኞች በማሠልጠኛ ማዕከሉ የሚሠጡ ስልጠናዎችን በስነ ምግባር፣ በሞራል እና በብቃት መወጣት አለባቸው።

እየተሠጠ ያለው ስልጠና ከሌሎች የሠራዊት ክፍሎች ጋር በመሆኑ የተሞክሮ እና የልምድ ልውጥ ለማድረግ ዕድል ይፈጥራል ያሉት ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ÷ ሰልጣኞች ያገኙትን ዕውቀት ለሎች ለማካፈል ተግተው ሊሰለጥኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በስልጠና ላይ የሚገኙ የማሪን ኮማንዶ ሰልጣኞች ቀጣይ ለሚሰጡ ስልጠናዎች አቅም ፈጣሪ በመሆናቸው ከማሰልጠኛው የሚያገኙትን ዕውቀት አቅበው ባህር ኃይልን ለማዘመን በሚሰራው ስራ ላይ የድርሻቸውን ለመወጣት እንዲዘጋጁ አስገንዝበዋል፡፡

የኮማንዶ እና አየር ወለድ ኃይል ማሰልጠኛ ማዕከል አዛዥ ኮሎኔል ቦጃ አጋ በበኩላቸው÷የባህር ኃይል ማሪን ኮማንዶ ሰልጣኞች በስነ ምግባርም ሆነ በማንኛውም እንቅስቃሴ አርዓያ መሆናቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በአዲስ መልክ ከተመሠረተ ጀምሮ የተለያዩ አቅም ፈጣሪ ስልጠናዎችን ከሀገር ውጭ እና በሀገር ውስጥ አባላቱን በማሠልጠን ላይ እንደሚገኝ መገለጹን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version