Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የደቡብ ምዕራብ ክልል የጸጥታ ምክር ቤት በወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ አስቀመጠ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የጸጥታ ምክር ቤት ወቅታዊ ክልላዊ የጸጥታ ሁኔታዎችን በመገምገም የተለያዩ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ።

ምክር ቤቱ በግምገማዉ፥ በ2014 በጀት ዓመት የተከናወኑ የሠላምና ጸጥታ ሥራዎች ላይ በቤንች ሸኮ፣ በሸካ በምዕራብ ኦሞ ዞኖች ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ገልጿል፡፡

በክልሉ ቀጣይ የሠላምና ጸጥታ ተግባራትንም ከፌደራል መንግስት ጋር በመሆን በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግም ነው የተመለከተው፡፡

በምዕራብ ኦሞና በካፋ ዞን  የአርብቶ አደር ቀበሌዎች አካባቢ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ዘረፋና ግጭቶችን መከላከል ላይ ተወያይቷል፡፡

በአካባቢው ዘላቂ ሠላም ለማስፈን እንዲቻል የመንገድና የማህበራዊ ተቋማት መሠረተ ልማት አቅርቦት ትኩረት እንዲሰጠው አቅጣጫ መቀመጡ ተመላክቷል፡፡

ያልተቋጩ የመዋቅር ጥያቄዎችን በሚመለከት ክልሉ የህዝብ ነጻ ፍላጎትን መሠረት በማድረግ ምላሽ እንደሚሰጥ ተገልጿል።

 

ጉዳዩን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ የሚሞክሩ አካላት እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለዉም ምክር ቤቱ ገምግሟል ነው የተባለው።

 

በማህበራዊ ሚዲያ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት  የሚደረግ ዘመቻ ላይ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

 

ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ እና የወርቅ አዘዋዋሪዎች ላይ ክትትል በማድረግ በየደረጃው የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥም  አቅጣጫ መቀመጡን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version