አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በ8 ወረዳዎች በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ሳቢያ ከ74 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ የተመራ ልዑክ ጉዳቱ በደረሰባቸው አካባቢዎች ተገኝቶ ምልከታ አድርጓል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በጎርፍ አደጋው ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለማድረግ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ በዚሁ ጊዜ ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ በበኩላቸው ÷በክልሉ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በርካታ ነዋሪዎችን ከቤት ንብረታቸው እንዳፈናቀለ እና በሰብልና እና በንብረት ላይም ከባድ ጉዳት እንደደረሰ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
በጎርፉ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከጋማቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

