አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ጥረቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ከትምህርት ሚኒስቴርና ከሀገር አቀፍ ፈተናዎች አገልግሎት የሥራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይቷል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሚኒስቴሩ እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ጠቅሰው ፥ ውጤታማነቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
በመድረኩ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና አሰጣጥ ዝግጅት፣ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና አሰጣጥ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ተቋማዊ ለውጥ፣ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ ስለተያዘው ዕቅድና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዋነኝነት ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ በስነምግባር የታነፀ ትውልድን ለመገንባት በትምህርት ሚኒስቴር የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራና ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ስለመኖራቸውም ተገልጿል።
የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ማንደፍሮ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆኑ መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና አሰጣጥ በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል መንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር በቅንጅት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተነናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች የልፋታቸውን ውጤት ብቻ የሚያገኙበት እንዲሆን እንደከዚህ በፊቱ ለፖለቲካ አጀንዳ እንዳይሆን ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ ፥ በቋሚ ኮሚቴው የተቀመጡትን አቅጣጫዎች በመቀበል በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

