Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቀውስ ጊዜ ዘገባና የመረጃ ስርዓት በጥንቃቄ መመራት እንዳለበት ማሳሰቢያ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ተቋማት የቀውስ ጊዜ ዘገባና የመረጃ ተደራሽነት ብሔራዊ ጥቅምን ታሳቢ ያደረገና በጥንቃቄ የሚመራ ሊሆን እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አሳሰበ።

ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የፌዴራልና የክልል የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ጉባኤ ተጠናቋል።

ጉባዔው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የፌዴራልና የክልል የኮሙኒኬሽን ዘርፎች የ2014 በጀት ዓመት የስራ አፈጸጻምና የ2015 ዕቅድ ላይ ተወያይቷል።

የመንግስት ኮሙኒኬሸን የቀጣይ 5 ዓመታት ረቂቅ ስትራቴጂ ሰነድ እና በመንግስት ኮሙኒኬሸንና የክልል የዘርፉ መዋቅሮች የስራ ግንኙንት ላይ በተዘጋጀ የመግባቢያ ሰነድ ላይም መክሯል።

የክልል ኮሙኒኬሽን ተቋማት በፌዴራል መንግስት የሚገለጹ መረጃዎችን የሚለቁበት አግባብ የአሰራር ስርዓት ሊዘረጋለት እንደሚገባም በጉባኤው ተመላክቷል።

የክልል የኮሙኒኬሸን መዋቅሮች ያልተናበቡና ያልተቀናጁ መረጃዎችን ከመስጠት እንዲቆጠቡና ፈቃድ ያልተሰጣቸው ሚዲያዎች በመንግስት ሁነቶች ላይ የሚሳተፉበት ዕድልም ሊስተካከል ይገባል ነው የተባለው።

በተለይ አገር ቀውስ ሲገጥማት የሚዲያና ኮሙኒኬሸን ዘርፉ ላይ ያለው የመረጃ ፍሰት ጥንቃቄ እንደሚሻ በአጽንኦት ተገልጿል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ÷ ለአገርና ህዝብ ጥቅም ሲባል የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ እንዲጠናከር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ጠንካራ የኮሙኒኬሽን ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል የኮሙኒኬሽን ፖሊሲና ስትራቴጂ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ደሲሳ በበኩላቸው÷ የህዝብ መረጃ የማግኘት መብት መገደብ ስለሌበት ተቋማት በየወቅቱ ለሚዲያዎች መረጃ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተቋማት ላይ ጠንካራ የምርመራ ጋዜጠኝነት እንዲሰራ የመንግስት ጽኑ ፍላጎት መሆኑን ጠቅሰው፥ ከወዲሁ ግልጽ መረጃ ለመስጠት መዘጋጀት አለባቸው ነው ያሉት።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትም ከክልሎች ጋር ደረጃውን በጠበቀና ወጥነት ባለው አግባብ ተናብቦ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

Exit mobile version