አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሕፃናትን ለውትደርና ሲያሰልፍ እና በጦር ጋሻነት ሲጠቀም ከማውገዝ ይልቅ በዝምታ በማለፉ ወቀሳ ቀረበበት።
በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ታዋቂው መምህርና የሕግ ምሁሩ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፥ አሸባሪው ህወሓት ሕፃናትን በጦር አውድማ ሲያሰልፍ ዝምታ የመረጠውን የባይደን አስተዳደር ኮንነዋል።
ወትሮም ቢሆን ለሕፃናትና ታዳጊዎች ግድ የሌለው አሸባሪው ህወሓት በአካልና በአዕምሮ ያልጠነከሩ ሕፃናትን ለውትድርና መልምሎ ወደ ጦር አውድማ እየማገዳቸው ይገኛል።
በሰብዓዊ መብት፣ በፕሬስ ነፃነት እና በአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋችነታቸው የሚታወቁት ዶክተር ቫን ቴራራ በበኩላቸው፥ አሸባሪው ህወሓት ሕፃናትን ለጦርነት እየተጠቀመባቸው እንደሚገኝ ሰሞኑን በትዊተር ገፃቸው ይፋ ማድረጋቸውን የኢዜአ ዘገባ አስታውሷል።
ዶክተር ቫን ቴራራ በጽሑፋቸው፥ የህወሓት እኩይ ድርጊት በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።
ሕፃናትን ለውትድርና መጠቀም የጦር ወንጀል በመሆኑ ድርጊቱን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊያወግዘው እንደሚገባም ነው የተጠቆመው።

