አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሌሎች ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር አስፋላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አስታወቀ፡፡
ክልሉ በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ ባወጣው መግለጫ÷ከግጭትና ጦርነት ውጪ መኖር የማይችለው አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያ መንግሥት የተዘረጋለትን የሰላም እጅ አሻፈረኝ በማለት በአማራና አፋር ክልሎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ወረራ በፅኑ አውግዟል፡፡
የሽብር ቡድኑ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን የተሰጠውን ተልዕኮ እየተቀበለ ሀገራችን በብሔር፣ በሐይማኖት እና በጎሳ ሲከፋፍል መኖሩም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
የክልሉ መንግስት መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ላይ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ!
አሸባሪው ህወሓት የሀገራችን ህዝቦችን እርስ በርስ በማናከስ አንድነታችንን ለመናድ ያልፈነቀለዉ ድንጋይ አልነበረም፡፡
አሸባሪዉ የህወሓት ቡድን ከታሪካዊ ጠላቶቻችን የተሰጠዉን ተልዕኮዎችን እየተቀበለ ሀገራችን በብሔር፣በሐይማኖትና በጎሳ ሲከፋፍል ኖሯል ፡፡
ኢትዮጵያዊን የምንታወቅበትን አብሮና ተቻችሎ የመኖር ዉድ እሴቶቻቸን ለመሸርሸር ያልሸረበዉ ሴራ አልነበረም። ኢ_ፍትሃዊነትን፣የኢኮኖሚ አሻጥሮችንና በታሪክ ፊት ዘግናኝ የሚባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ጭምር በዜጎቻችን ላይ ፈጽሟል።
የሀገራዊ አንድነትን ለማፍረስ ሲዖል ድረስ እንደሚጓዝ ግልፅ በማድረግ የኢትዮጵያና የኢትዮጵዊያን ቁጥር አንድ ጠላት መሆኑን አረጋግጧል ፡፡
የንፁሃን ዜጎቻችን ደም አፍሷል፤ንብረት አውድሟል፤ የትግራይ ወጣቶችን በእሳት ማግዷል፡፤ ብዙዎችን አፈናቅሏል።ወትሮም ቢሆን የሠላም አማራጭ የሚያንገሸግሸዉና ያለጦርነት ዉጭ ዉሎ ማደር የማይችለዉ ይህ ቡድን በሀገራችን መንግስት በኩል የቀረበዉ የሠላም አማራጭ አሻፈረኝ ብሎ ሶስተኛ ዙር ወረራ በአማራና በአፋር ክልሎች በይፋ ጦርነት ከፍቷል።
በዚህም ለሠላም መፍትሄ ዓይኑ የታወረ፣ጆሮ የተደፈነ መሆኑን አስመስክሯል። ህወሓት ሕፃናትን ከፊት ለፊት በማሰለፍ የጥይት ቀለብ በማድረግ ሰብዓዊነት ፈጽሞ የማይሰማዉ በጭካኔ በየተሞላ ቡድን መሆኑን በገሃድ አስመስክሯል።
ከግጭትና ጦርነት ውጪ መኖር የማይችለው አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያ መንግሥት የተዘረጋለትን የሰላም እጅ አሻፈረኝ በማለት በአማራና አፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ላይ እየፈፀመ ያለውን ወረራ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት በፅኑ ያወግዛል፡፡
የክልላችን መንግስትም የሀገራችን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከሌሎች ኢትዮጵያ ወዳድ ወንድሞችና እህቶች ጎን በመሆን አስፈላጊውን ሁሉን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ይህ አሸባሪ ቡድን የኢትዮጵያ መንግስት የዘረጋውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበል አለማቀፉ ማህበረሰብም ግፊት ሊያደርግ ይገባል፡፡
ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት
ነሐሴ 22, 2014
ቦንጋ