Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዶክተር ሙላቱ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን አቋም የሚያስረዳ መልዕክት ለአውሮፓ ህብረት መሪዎች እና ለፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት አደረሱ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን ግልጽ አቋም የሚያስረዳ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተላከ መልዕክት ለአውሮፓ ህብረት መሪዎች እና ለፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት አደረሱ።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ለአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሚካኤል የተላከውን መልዕክት ለካቢኔ ሃላፊው ፍራንኮስ ሩክስ እና ለአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮንደር ለይን የተላከውን መልዕክት ለአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል አድርሰዋል።

እንዲሁም ለፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት የተላከውን መልዕክት ለፕሬዚዳንቱ የአፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ፍራንክ ፓሪስ ማድረሳቸው ነው የተነገረው።

ዶክተር ሙላቱ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እና ከፈረንሳይ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በነበራቸው ቆይታ ከግብፅና ሱዳን ጋር እየተካሄደ በሚገኘው ድርድር ኢትዮጵያ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ መፍትሄ ለማምጣት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የከፋ ጉዳትን የሚያስከትል ሳይሆን ምክንያታዊ እና ተመጣጣኝ የውሃ አጠቃቀም መርህን እንደምትከተልም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከግብጽ እና ከሱዳን ጋር በፈረንጆቹ 2015 በደረሰችው የመርህ ስምምነት መሰረት ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን በቅርቡ የመጀመሪያውን ውሃ በመሙላት ሀይል ለማመንጨት የሚያስችል አስፈላጊ ስራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለችም ብለዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ እየተካሄደ ከሚገኘው የሶስትዮሽ ውይይት እንዳልወጣች በማስረዳት በሀገር ውስጥ ተጨማሪ ውይይቶችን ለማድረግ ለሶስቱ ሀገራት ተጨማሪ ጊዜ መጠየቋን ነው ያስረዱት።

Exit mobile version