Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ዜጎች የጠላትን ፕሮፖጋንዳ ወደጎን በመተው ከጠላት ጋር እየተፋለመ ለሚገኘው ጥምር ጦር ደጀንነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ የክልሉ ሕዝብ እና መላ ኢትዮጵያውያን የጠላትን የተለመደ ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ወደጎን በመተው ከጠላት ጋር እየተፋለመ ለሚገኘው ጥምር ጦር ህዝባዊ ደጀንነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቀረቡ፡፡

በአንድነትና በጽናት የጠላትን እንቅስቃሴ ቀልብሰን በቅርብ ለድል እንበቃለን፤ እናሸንፋለንም ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።

ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ እድሜ ዘመኑን ሙሉ ከሰላም ይልቅ ጦርነትን እንደ መልካም አማራጭ የሚቆጥረው ወያኔ በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ ዳግም ወረራ መፈጸሙን አንስተዋል፡፡

ወራሪው ቡድን ከኢትዮጵያ ሰላም ይልቅ መከፋፈልን፣ ከሕዝብ አንድነት ይልቅ ጥላቻና ልዩነትን ዘርቶ ሲኮተኩትና ሲንከባከብ የኖረ ቡድን መሆኑን ገልጸው፥ ጥፋትን እንጂ ፈጽሞ የሰላም መንገድን መርጦም ሆነ ተከትሎ አያውቅም ነው ያሉት።

የዚህን የሽብር ቡድን ወረራ ለመቀልበስ ጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሺያና ፋኖ በጀግንነት እና በቆራጥነት ስሜት እየተፋለሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጥምሩ ጦር የወያኔን ቀቢጸ ተስፋ አምክኖ ለድል መብቃት በሚችልበት አስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኝም አውስተዋል፡፡

ስለሆነም የአማራ ክልል ሕዝብና መላ ኢትዮጵያውያን፥ የጠላትን የተለመደ ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ወደጎን በመተው ከጠላት ጋር እየተፋለመ ለሚገኘው ጥምር ጦር ሕዝባዊ ደጀንነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Exit mobile version