Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አንቶኒዮ ጉተሬዝ  የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድ ፍላጎት እንዳላቸው ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድ ፍላጎት እንዳላቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ገለፁ፡፡

የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ለደህንነት ዋስትና የማይሰጡ፥ ነገር ግን ጥፋትን ብቻ የሚያመጡ ተደርገው በታሪክ መመዝገብ አለባቸው ሲሉ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ተናግረዋል።

“ዓለማችን በኒውክሌር ጦር መሳሪያ ታግታ ቆይታለች” ሲሉም ነው ጉተሬዝ በትዊተር ገፃቸው ያሰፈሩት።

መሳሪያዎቹን “የሞት መሳሪያ” በማለት የገለጿቸው ሲሆን በንድፍ ውጤታቸው ጥፋት ብቻ በመሆኑ እነዚህን መሳሪያዎች የያዙ ሀገራትም ድል እና ደህንነትን ማረጋገጥ አይችሉም ሲሉ ዋና ፀሀፊው ተናግረዋል።

“የሰው ልጅ አንድም ባለመግባባት ፣ አንድም በተሳሳተ ስሌት ከኒውክሌር እንዳይርቅ ሆኗል” ያሉት ጉተሬዝ፥  በዩክሬን ውስጥ ያለው ግጭት፣ በሌሎች አካባቢዎች ያለው የአየር ንብረት ቀውስ እና የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ተደማምረው ዓለምን ከመቼውም የበለጠ ውጥረት ውስጥ በመክተት ፊት ለፊታችን ተጋርጠዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

ይህንንም አስመልክተው ዋና ጸሐፊው በነሐሴ ወር መጀመሪያ  በኒውዮርክ በተካሄደው ኑክሌርን  ያለመስፋፋት ስምምነት (ኤንፒቲ) ግምገማዊ ኮንፈረንስ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ “ የኑክሌር ጦር መሣሪያዎችን ማስወገድ በፍፁም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማድረጊያ ብቸኛው ዋስትና ነው” ነበር ያሉት።

በአሁኑ ጊዜ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎች በአሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ሩሲያ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ፓኪስታን፣ ህንድ፣ እስራኤል እና ሰሜን ኮሪያ እጅ ይገኛሉ።

የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት እንደገለጸው፥  “በ2022 መጀመሪያ ላይ ከነበሩት 12ሺህ 705 የጦር መሳሪያ ስብስቦች አጠቃላይ ዝርዝር ውስጥ 9 ሺ 440  ያህሉ በወታደራዊ  ተቋማት ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ” ማለቱን የአርቲ ዘገባ አመላክቷል።

Exit mobile version