አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ 672 ሚሊየን ብር ወጪ የሚገነባው የጅግጅጋ ከተማ ማሳለጫ መንገድ ግንባታ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
የመንገድ ግንባታውየከተማዋን የትራፊክ መጨናነቅና አደጋ ለመቅረፍ ታልሞ ነው የሚገነባ መሆኑም ተነግሯል፡፡
30 ሜትር የጎን ስፋት እና ሰባት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቱ የፌደራል መንግስት በመደበው 672 ሚሊየን ብር ወጪ እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው የተገለፀው።
መንገዱ አንድ ዋና ማሳለጫ ሲኖረው ተሽከርካሪዎች ከተማ ውስጥ መግባት ሳያስፈልጋቸው አልፈው እንዲሄዱ የሚያገለግል ነው።
በእስካሁኑ የግንባታ ሂደት የአፈር ቆረጣና ሙሌት፣ የሰብቤዝ፣ የውኃ መፋሰሻ ቱቦ ቀበራና የ94 ሜትር ድልድይ ሥራዎች እና አስፋልት ለማንጠፍ የሚረዱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን የመንገዶች አስተዳደር መረጃ ያመላክታል፡፡
በእስካሁኑ የግንባታ ሂደት የሲሚንቶ ዕጥረት ያጋጠመ ሲሆን ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ተብሏል።
መንገዱ በኮንክሪት አስፋልት ደረጃ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን፥ የእግረኛ እና የብስክሌት መተላለፊያ እንዲሁም የአረንጓዴ ሥፍራ ይኖረዋል።
የጅግጅጋ ማሳለጫ መንገድ ግንባታ ሲጠናቀቅ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በማሳለጥ ለከተማዋ ዕድገት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
በክልሉ ለሚደረጉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችም የጎላ ሚና እንደሚኖረው ነው የተገለፀው፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

