Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አዲሱን ዓመት የምንቀበለው ለስኬት ያበቁንን እሴቶች በማጎልበት ነው -መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲሱን ዓመት የምንቀበለው ለስኬት ያበቁንን ተሞክሮች እና እሴቶች በማጉላትና የተጋረጡብንን ፈተናዎች በድል ለመወጣት የሚያስችሉ መደላድሎችን በሚፈጥር መልኩ ነው ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም፥ የ2015 ዘመን መለወጫን ስንቀበል ለስኬት ያበቁንን ተሞክሮች እና እሴቶች በማጉላትና በመቀመር ለተጨማሪ ድሎች እንዲሁም አሁንም የተጋረጡብንን ፈተናዎች በድል ለመወጣት የሚያስችሉ መደላድሎችን በሚፈጥር መልኩ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም አዲሱን ዓመት ለመቀበል አምስቱ የጳጉሜን ቀናት የሚከበሩበት መሪ ቃል እና ስያሜ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መፅደቁን ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስታወቁት፡፡

በዚህም መሰረት አምስቱ የጳጉሜን ቀናት” ጳጉሜን በመደመር” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ጳጉሜን 1 የበጎ ፈቃድ ቀን፣ ጳጉሜ 2 የአምራችነት ቀን፣ ጳጉሜን 3 የሰላም ቀን፣ጳጉሜን 4 የአገልጋይነት ቀን እንዲሁም ጳጉሜን 5 የአንድነት ቀን በሚል ስያሜ እንደሚከበርም ገልፀዋል፡፡

ይህን ተከትሎም በእያንዳንዱ የጳጉሜን ቀናት ከቀናቱ ስያሜ ጋር የተገናኙ መርሐ ግብሮች እና ተግባራት ይኖራሉ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም፥ 2014 ዓ.ም ፈተናዎች የበዛበት፥ ነገር ግን በበርካታ አኩሪ ድሎች የታጀበ ነበር ብለዋል፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት ድርቅ ፤ጦርነት እና የኑሮ ውድነት ፈተናዎች እንደነበሩ ያነሱ ሲሆን ÷ አሸባሪው ህወሓት የከፈተው ጦርነት መቀልበሱን እና ሕዝብን ከብተና ማዳን መቻሉን የ2014 ስኬት መሆኑን አውስተዋል፡፡

እንዲሁም አልሸባብ የሽብር ቡድንን መከላከል መቻሉና ሽንፈትን ተከናንቦ ወደ መጣበት መመለስ መቻላችን ፣ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናክሮ መቀጠሉ፣ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መከናወኑ እና ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመሩ፣ ሀገሪቱ በምግብ እራሷን እንድትችል ተደረገውን ጥረት በዓመቱ የተከናወኑ ስኬቶች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎቸው ያሉ ዜጎች ህይወታቸው ለአደጋ እንዳይጋለጥ ህይወት የማዳን ስራዎች መሰራታቸውንም አስረድተዋል።

ዓለምን ባስደመመው አራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲሁ 25 ሚሊየን ችግኝ መትከል መቻሉ በ2014 ዓ.ም ከነበሩ ስኬቶች የሚጠቀሱ መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት፡፡

በፌቨን ቢሻው

Exit mobile version