አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ በኩል የህወሓት ጀሌዎች በሆኑት አልሸባብና ሸኔ የሽብር ቡድኖች የሚደረጉ ሙከራዎችን በማክሸፍ በህወሃት ላይ ለሚወሰደው እርምጃ እንደሁልጊዜው ያልተቆጠበ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የከተማ አስተዳደሩ ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫው፥ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የያዘው እኩይ ዓላማ ለአገራችን ሁለንተናዊ ሰላምና ልማት ፀር መሆኑን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና ህዝብ ይገነዘባል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም ያረጋግጣል ብሏል በመግለጫው፡፡
የከተማ አስተዳደሩ መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
አሸባሪው የህውሓት ቡድን ለ27 ዓመታት የአገሪቱን ማእከላዊ ስልጣን ተቆጣጥሮ በነበረበት ጊዜ ከፈጸማቸው ኢሰብአዊ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዋነኛ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የድሬደዋ አስተዳደር ህዝብ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ቡድኑ የአገሪቱ ፈላጭ ቆራጭ ገዢ በነበረበት ዘመን የፍቅር ፣ የመቻቻል እና የብሄር ብሔረሰቦትች የአብሮነት መኖሪያ ትንሿ ኢትዮጵያ የሆነውን የድሬደዋ አስተዳደር ህዝብን እርስ በእርስ እንዲጠራጠር እና እንዲጋጭ በማድረግ በማህበረሰቡ መካከል አለመተማመን እንዲፈጠር አርጓል፡፡
አሸባሪው ህውሀት በፍቅር መሀል ጥላቻን በመተማመን መሀል መጠራጠርን በአንድነት መሀል መከፋፈልን በበጎነት መሀል ክፋትን በሰላም መሀል ጦርነትን የሚዘራ ባጠቃላይ ከሰው ልጆች መሰረታዊ እና ሰዋዊ ባህሪ ያፈነገጠ ፀረ -ሰው ድርጊት የሚፈፅም መሰሪ ስብስብ ነው ።
ከዚህም አልፎ ለርካሽ ፖለቲካና ለስልጣኑ ቀጣይነት ሲል ሴራ በመጎንጎን የስልጣኔ በር የፍቅር እና አብሮ መኖር ተምሳሌት የሆነችውን ድሬደዋን ስምና ዝናዋን በማይመጥን ደረጃ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ማሽቆልቆል እዲፈጠርና አስተዳደሩ በልማት ወደ ኋላ እንዲቀር አድርጓል፡፡
አሸባሪው ህውሓት ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እየተጋለበ በከፈተው ጦርነት በአማራ እና አፋር ክልሎች የሚኖሩ በርካታ ንፁሃን ዜጎችን ህይወት አጥፍቷል፤ በእድሜ ልክ ድካም የተከማቸ የሚሊዮኖችን ሀብትና ንብረትም በከንቱ አውድሟል።
የዚህ ባንዳ ቡድን ዋነኛ ሀሳብ ኢትዮጵያን እኔ ወይም የኔ ተላላኪ የሆነ ሀይል ካልመራት አፈርሳታለሁ የሚል ሲሆን ይህን በጤነኛ አእምሮ ሊታሰብ የማይችል ከክፋት ሁሉ የከፋ ሀሳቡን ለማስፈፀምም ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት በመክፈት ምስኪን የደሀ ልጆችን በአደንዛዥ እፅ እያደነዘዘ ወደ እሳት እየማገደ ይገኛል።
ቡድኑ የያዘው እኩይ አላማ ለአገራችን ሁለንተናዊ ሰላም እና ልማት ፀር መሆኑን የሚገነዘበው የድሬደዋ አስተዳደር መንግስት እና ህዝብ በምስራቅ በኩል የህወሃት አጋሮች በሆኑት እንደ አልሸባብ እና ሸኔ ባሉ የሽብር ቡድኖች የሚሞከሩ ሙከራዎችን በማክሸፍ እና በህወሃት ላይ በሚወሰደው እርምጃ እንደሁልጊዜው ያልተቆጠበ ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በአፅንኦት እየገለፀ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር አስፈላጊውን መሰዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም ያረጋግጣል፡፡
በመጨረሻም ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ቡድኑ የጀመረውን ጦርነት አቁሞ በኢትዮጵያ መንግስት የቀረበውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበል ተገቢውን ጫና እንዲያሳድር የድሬደዋ አስተዳደት ጥሪውን ያቀርባል።
የድሬደዋ አስተዳደር
ነሐሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም
ድሬዳዋ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

