አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጀጎል ግንብ ውስጥና ዙሪያ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ ላይ የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎች እንዲጠናከሩ የሐረሪ ክልል ካቢኔ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
የክልሉ ካቢኔ የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ የተቀናጀ ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ እና የሐረር ከተማ ማዘጋጃቤታዊ ገቢን ለማሳደግ በቀረቡለት ሰነዶች ላይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ለጀጎል ዓለም ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ የቀረበው ሰነድ የጀጎል ቅርስ ዓለም አቀፍ ቅርስነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ያግዛል ተብሏል።
ከቅርሱ ጋር በተያያዘም በጀጎል ውስጥና በጀጎል ግንብ ዙሪያ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ ግንባታ የመሬት ወረራ ላይ የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎች እንዲጠናከሩ ካቢኔው አቅጣጫ አስቀምጧል።
የሐረር ጀጎል የዓለም ቅርስ ስፍራን ለመንከባከብና ለመጠበቅ አስፈላጊ የሆኑ የሕግ ማእቀፍ፣ የአደረጃጀት፣ የሰው ኃይል፣ የግብዓት እና ሌሎች የሕግ የአፈጻፃም ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ግብረ ኃይል መቋቋሙም ተገልጿል።
የከተማ ማዘጋጃቤታዊ ገቢ በተሻለ የአሠራር ስርዓት መሰብሰብና ማስተዳደር የክልሉን ገቢ ለማጎልበት እና የመሰረተ ልማት አገልግሎቶችን ለማስፋት ወሳኝ ሚና ስላለው የተበታተነውን የአገልግሎት ገቢ በአንድ ቋት ለመሰብሰብ ይረዳልም ተብሏል፡፡
በክልሉ ማዘጋጃቤታዊ ገቢ አቅም ለማሳደግና የገቢ አሰባሰብ ስርአቱን በማዘመን ገቢን አሟጦ መሰብሰብ እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን የሐረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

