አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት ሕጻናትን አስገድዶ በጦርነት በማሰለፍ የሚያከናውነውን ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተገቢው መልኩ እያወገዘው አለመሆኑ ተገለጸ፡፡
የፖለቲካ ተንታኙ አንድሪው ኮሪብኮ እንደገለጹት÷ አሸባሪው ህወሓት ሕጻናትን አስገድዶ በጦርነት በማሰለፍ ለሰው ማዕበል የጦርነት ስልት እየተጠቀመባቸው ቢሆንም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ የሚጠበቅበትን ምላሽ እየሰጠ አይደለም፡፡
ስነ ምግባር ያለው ወታደር ሕጻናትን ተኩሶ እንደማይገድል ገልጸው÷ የሽብር ቡድኑ ማፊያዎች ይህን ከግንዛቤ በማስገባት ሕጻናትን በጦርነት በማሰለፍ ለሽብር ተግባራቸው እውን መሆን እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡
ቡድኑ ሕጻናትን በጦርነት የሚያሰልፈው በወታደሩ ዘንድ “ራስን በመከላከልና ሕጻናትን ተኩሶ አለመግደል” በሚለው የሞራል እሳቤ ላይ ውዥንብር ለመፍጠርና ዓለማውን ለማሳካት መሆኑንም ነው የጠቀሱት፡፡
ኢትዮጵያ ለመልማት የምታደርገውን ጥረትና በዓለም አቀፉ መድረክ ያላትን ሚዛናዊ አካሄድ የማይፈልጉ የውጭ አካላት ጦርነቱ እንዲባባስ እየሠሩ መሆናቸውንም አንድሪው ኮሪብኮ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
የፌደራል መንግሥት ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ረዥም ርቀት ቢጓዝም የሽብር ቡድኑ ግን ጥቃትን በመፈጸም ችግሮች እንዲባባሱ ማድረግ ሆኗል ነው ያሉት፡፡
መንግሥት ሰላማዊ ዜጎች እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ቢያደርግም÷ አሸባሪው ህወሓት ግን ሕዝብን እንደ ምሽግ በመጠቀምና የሕዝባዊ ማእበል የጦርነት ስልትን እየተከተለ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሽብር ቡድኑን አካሄድ በግልጽ አለማውገዙ ደግሞ እጅግ አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክ የአፍሪካ ድምጽ እንዲሰማ እንዲሁም በዓለም ጂኦ ፖለቲካ ባለው የምስራቅና ምዕራብ መሳሳብ ውስጥ ሚዛኗንና ነጻነቷን ጠብቃ በመንቀሳቀሷ በአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት ጥርስ እንደተነከሰባት አመላክተዋል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን ጨምሮ መሰል የቡድኑ ደጋፊዎች የዓለም አቀፍ ተቋማትን ሚና በመጥለፍ የግል ፍላጎታቸውን እያራመዱ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

