አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአንበሳ እና ሸገር አውቶብስ አገልግሎት ድርጅቶች የተሳፋሪዎችን ንጽህና ለመጠበቅ ከዛሬ ጀምሮ የእጅ ማጽጃ አልኮል እንደሚያቀርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገለፁ።
አሽከርካሪዎቹ የእጅ ጓንት የሚጠቀሙ ሲሆን ተሳፋሪዎችም ወደ አውቶቡሶች ሲገቡ ድርጅቱ የሚያቀርበውን የእጅ ማጽጃ አልኮል እጃቸው ላይ አድርገው እንዲገቡ በፌስቡክ ገፃቸው አሳስበዋል።
ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ ኃይልም በከተማዋ ጠንካራ ቁጥጥር እያካሄደ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት።
የህዝብ አገልግሎት ሰጪዎችና በጎ ፈቃደኞችም አቅም የሌላቸውን እንዲሁም ውሀና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ማግኘት የማይችሉትን በተቻለን መንገድ እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።
በዛሬው እለት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እንዲረዳ ለ15 ቀናት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ ስፖርታዊ ውድድሮችና ህዝባዊ ስብሰባዎች እንዳይደረጉ መወሰኑ ይታወሳል።

