Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት የአገርን ጠላት በጋራ ከመመከት አይገታንም – ዶ/ር በለጠ ሞላ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፖለቲካ አመለካከት፣ ወቅታዊ ችግሮች እና የሀሳብ ልዩነት የአገርን ጠላት በጋራ ከመመከት አይገታንም ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ገለጹ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሠራተኞች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን÷ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ጦርነት ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ብቻ የሚደረግ ጦርነት አይደለም ተብሏል።

በውይይቱ ወቅት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ እንደተናገሩት÷ እየተካሄደብን ያለው ጥቃት በሌሎች አገራት በቴክኖሎጂ፣ በሀሳብና በፋይናንስ የሚታገዝ በሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ወረራ  ነው፡፡

ይሄን ተግባር በግልጽም በድብቅም መደገፍ የአገር ክህደት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ÷ የአገር ክህደትን ደግሞ ቆሞ መመልከት አይገባም ሲሉ አስገንዝበዋል።

ከወቅታዊ ችግር በላይ ይህን የጋራ ችግር ለመፍታት የሚደረገውን መስዋዕትነት መደገፍና መደበኛ ስራን በትኩረት በመስራት አጋርነታችንን ማሳየት መቻል አለብን ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ያለቅድመ ሁኔታ ለሰላም ውይይት አቋሙን በተደጋጋሚ ገልጿል ያሉት ሚኒስትሩ÷ የህወሓት ቡድን የሰላም አማራጭን ወደ ጎን በመተው ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ጦርነት መግቧቱን ገልጸዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለትግራይ ሕዝብ ሠላም የማያመጣ፣ የሕዝብ ጥያቄን የማይመልስና ሰብዓዊ ውድመት እየፈጸመ የሚገኝ ነው ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በሽብር ቡድኑና በውጭ ጠላቶቻችን የተቃጣብንን ጥቃት በጋራ በመቆም  ወረራውን  መቀልበስ  እንደተቻለ አስረድተዋል።

ዘንድሮም በጋራ በመቆም የተከፈተብንን ጥቃት ቀልብሰን፥  የኢትዮጵያን አንድነት ማስቀጠል አለብን ነው ያሉት።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው÷ጥቃቱን ለመመከት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ማለታቸውንም ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

Exit mobile version