Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የደቡብ ክልል ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ብሄሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመምከር ውሳኔ አሳለፈ።

የደቡብ ብሄሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ዛሬ ባካሔደው 247ኛ መደበኛ ስብሰባው በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት መክሯል።

ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ መንግስት ለሰላም ያለውን ፅኑ አቋም በተኩስ አቁም ማሳየቱን እና አርሶ አደሩ ከነበረበት የጦርነት ስጋት ወጥቶ ወደ ግብርና ስራው እንዲያተኩር ለማድረግ መንግስት የተኩስ አቁም ማድረጉም በውይይቱ ተነስቷል፡፡

ሆኖም ግን አሸባሪው ህወሓት መንግስት ለሰላም ያሳየውን ቁርጠኝነት ወደ ጎን በመተው ለሶስተኛ ጊዜ በህዝብ ላይ ግልጽ ወረራ መፈፀሙን ምክር ቤቱ ገልጿል።

መንግስት የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ብሎም በሀገሪቱ ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት ተገዶ የገባበትን ጦርነት መስተዳድር ምክር ቤቱ የሚደግፍ ሲሆን ሂደቱንም በቅርበት እንደሚከታተል አጽንኦት ሰጥቷል።

አሸባሪው ቡድን ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች እንዲሁም ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በማበር ሀገር ለማፍረስ እያደረገ ያለውን ወረራ መስተዳድር ምክር ቤቱ አውግዟል።

የክልሉ ሕዝብ በግምባር እየተፋለሙ ላሉ ጀግኖች÷ ስንቅ በማዘጋጀት፣ ወደ ግንባር በመዝመት እና የዘማች ቤተሰብን በመንከባከብ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

ህብረተሰቡ ከአሸባሪው ህወሓት እና ከሀገር አፍራሽ የመረጃ ምንጮች ከሚወጡ የሀሰት መረጃዎች በመቆጠብ መንግሥት የሚያስተላልፋቸውን መረጃዎች እንዲከታተል መስተዳድር ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምስረታ እና ነባሩን ክልል በአዲስ ክልል የማደራጀት ተግባር ማስፈፀሚያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ማቋቋሚያና የአሠራር ስርዓት መወሰኛ ደንብ ላይ ውሳኔ ማስተላለፉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ  መረጃ አመላክቷል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version