Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በክልሉ ለትምህርት ስራው ውጤታማነት የህብረተሰብ ትብብር መጠናከር አለበት – አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ለትምህርት ስራው ውጤታማነት ወላጆችን ጨምሮ የመላው ህብረተሰብ ትብብር እንዲጠናከር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ጥሪ አቀረቡ።

በትምህርት ዘመኑ እቅዱን ለማሳካት ከነሐሴ 30 እስከ ጳጉሜ 5 የሚቆይ “የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በጋራ እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ሀሳብ የትምህርት ንቅናቄ መርሐ ግብር ተጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ በንቅናቄው ማስጀመሪያ ላይ እንዳሉት ፥ የክልሉ የትምህርት ሽፋን ጥሩ መሆኑን ጠቁመው ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል።

ነባር፣ አዲስና ያቋረጡ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ በሚሰራው ስራም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በዚህም ለትምህርት ስራው ውጤታማነት ወላጆችን ጨምሮ የመላው ህብረተሰብ ትብብር እንዲጠናከር ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሴ ጋጄት በበኩላቸው ፥ በተያዘው የትምህርት ዘመን በቅድመ መደበኛ ፣በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ225 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።

ይህም ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ22 ሺህ 456 ብልጫ እንዳለው ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ንቅናቄውን የሚያስተባበሩ የክልሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ስምሪት በሁሉም ወረዳዎች እንደሚደረግም ገልጸው ፥ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናት የቤት ለቤት ምዝገባ እንደሚካሄድም ነው የተናገሩት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version