Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለ30 ቀናት የሚቆይ ሀገር አቀፍ የመንገድ ደህንነት ንቅናቄ ከነገ ጀምሮ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከነገ ጀምሮ ለ30 ቀናት የሚቆይ ሀገር አቀፍ የመንገድ ላይ የትራፊክ ቁጥጥር እና ግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ እንደሚካሄድ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ።

“አደጋውን ለመቀነስ እኔም ድርሻ አለኝ፣ ከጳጉሜን እስከ ጳጉሜን እንደርሳለን!” በሚል መሪ ሀሳብ ነው ንቅናቄው የሚካሄደው።

የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ጀማል አባሶ በሰጡት መግለጫ÷ ከነገ ጀምሮ እስከ መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም  የሚቆይ የመንገድ ደህንነት ንቅናቄ ለማከናወን ዝግጅቱ ተጠናቋል ነው ያሉት፡፡

አክለውም የጳጉሜን ቀናት በልዩ ሁኔታ ለመንገድ ደህንነት የግንዛቤ ንቅናቄ ለመጠቀም ዝግጅት መደረጉን ነው ያስረዱት።

የቁጥጥር መርሐ ግብር መዘጋጁቱን ጠቁመው፥  ቀላል የትራፊክ ሕግ ጥሰት ለፈጸሙ አሽከርካሪዎች የማስተማርና ምክር የመስጠት ተግባር እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም የትራፊክ አደጋን መከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ ውይይት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡

በትራፊክ አደጋ ምክንያት የደም እጥረት ላጋጠማቸው ሰዎች ደም የመለገስ፣ ለትራፊክ አደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች ድጋፍ የማድረግ እና ለአቤት ሆስፒታል የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ የመሰጠት  መርሐ ግብር መኖሩንም ነው የገለጹት፡፡

የፌደራል ፖሊስ ትራፊክ ቁጥጥርና አደጋ ምርመራ መምሪያ የስልጠናና ምክር አገልግሎት ዋና ክፍል ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ይስሃቅ ቱኬ በበኩላቸው÷ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ አሽከርካሪዎች የትራፊክ ሕግን በተገቢው መልኩ ሊተገብሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡም ኃላላፊነቱን በአግባቡ  እንዲወጣ ጥሪ መቅረቡን የኢዜአ ዘገባ ይጠቁማል፡፡

 

Exit mobile version