Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በህወሓት ምክንያት የትግራይ ህዝብ ለከፍተኛ ርሃብ ፣ ስቃይና እንግልት ተዳርጓል – ምርኮኞች

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ህወሓት ምክንያት የትግራይ ህዝብ ለከፍተኛ ርሃብ ፣ ስቃይና እንግልት ተዳርጓል ሲሉ እጃቸውን የሠጡ የቡድኑ ታጣቂዎች ተናገሩ፡፡

ኢትዮጵያን ለማፍረስ አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጥቃት እጃቸውን ከሰጡ ተዋጊዎች መካከል ሰለሞን ሺሻይ ፣ ተስፋልደት ግሩምና ሀለፎም ገ/መድህን እንደተናገሩት ፥ በኢዛና ፣ በህፃይና በእንዳባጉና ማሰልጠኛዎች ለወራት የተለያየ ወታደራዊ ስልጠናዎችን መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡

አክለውም ልክ የዛሬ ዓመት በአማራና አፋር ክልሎች ላይ እንደፈፀሙት ሁሉ አሁንም ሀገር ለማፍረስ፣ ህዝብን ለመግደልና ለማሰቃየት እንዲሁም ንብረት ለመዝረፍ በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ትዕዛዝ የማጥቃት ውጊያ ግዳጅ ተሰጥቷቸው እንደተሰማሩ ነው ያስረዱት።

“ያለንን አቅም ሁሉ ተጠቅመን ወልቃይትና ራያን አስመልሰን ታላቋ ትግራይን እንመሰርታለን” ብለን ጦርነት ብንከፍትም ያሰብነውን ሳናሳካ ሙት ፣ ቁስለኛና ምርኮኛ ለመሆን መገደዳቸውን የተናገሩት ምርኮኞቹ ፥ የሽብር ቡድኑ የትግራይ ወጣቶችና ታዳጊዎችን በየግንባሩ ለጦርነት በመማገድ ላይ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በፈቀደው አኳኋን በዓለምአቀፍ ድርጅቶች አማካኝነት የተለያዩ እርዳታዎችና ሰብዓዊ ድጋፎች ወደትግራይ ቢገቡም ቡድኑ ግን ግላዊ ጥቅምና ፍላጎቱን ለማሳካት ላደራጀው ተዋጊ ሀይል እያዋለው በመሆኑ በሽብር ቡድኑ ተግባር ምክንያት የትግራይ ህዝብ ለከፍተኛ ርሃብ ፣ ስቃይና እንግልት እንደተዳረገም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በሙሉ አቅሙ ቆርጦ የተነሳው የሽብርተኛው ህወሓት ኃይል በወልቃይት ግንባር በከፈተው ማጥቃት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንደደረሰበት መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version