አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ለአቅመ ደካሞች ቤቶችን አድሶ አስረከበ፡፡
ፓርቲው በአገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ የተከበረውን የበጎነት ቀን ምክንያት በማድረግ የ11 አባዎራዎችን ባለአንድ ወለል መኖሪያ ቤት አድሶ አስረክቧል፡፡
በርክክብ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና ርዕዮ ዓለም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ ባደረጉት ንግግር÷ ብልፅግና ሰው-ተኮር ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡
“በጎ ፈቃደኝነት አንዳችን ለሌላኛችን ተሳስበን የምንኖርበት መርህ ነው “ ያሉት አቶ አብርሃም ÷ በቀጣይ በጅምር ያሉ ሥራዎችን የማጠናቀቅ ሥራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል፡፡
የፈረሱ የአቅመ ደካማ ቤቶችን የማደስ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡
የሚያጋጥሙ ችግሮችን ሕዝብን ከጎናችን በማሰለፍ እንወጣለን ማለታቸውን ከብልፅግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የጽሕፈት ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች እና ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡

