አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከስዊዘርላንድ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሪ ዋልት ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸውም ሰዊዘርላንድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጊዜያዊ አባል ሆና በመመረጧ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት አስተላፈውላቸዋል።
ስዊዘርላንድ በፀታው ምክር ቤት ስብሰባዎች በሚነሱ ዓለም አቀፋዊ አጀንዳዎች ላይ አንደ ወትሮው ሁሉ ሚዛናዊና ምክንያታዊ የሆነ አቋሟን እንደምታንፀባርቅ ያላቸውን እምነትም ገልጸውላቸዋል።
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ስላለው ሁኔታ ገለፃ ያደረጉት አቶ ደመቀ፥ የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የሰላም ድርድር ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከሰላም ፍላጎቱ ጎን ለጎን፥ መንግስት ሕዝቡን ከአሸባሪው ህወሓት ጥቃት ለመከላከልና የአገሩን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ የሚያደርገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፥ ወደ የሰላም ድርድሩ ለመመለስ ዝግጁ መሆኑንም አብራርተዋል።
ሁለቱ አገሮች በንግድና በቱሪዝም ዘርፎች ያላቸውን የረዥም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር መስማማታቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ የተካሄደው የኢትዮጵያና ስዊዘርላንድ 5ኛው የጋራ የፖለቲካ የምክክር መድርክ፥ የአገራቱን የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነት በላቀ ደረጃ የማጠናከር ዓለማ እንዳለው ተገልጿል።

