Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ባለፈው በጀት ዓመት ከወርቅ ምርት ከ560 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጷጉሜን 2፣ 2014፣ (ኤፍ ቢ ሲ) በ2014 በጀት ዓመት ከወርቅ ምርት ከ560 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ባለፉት ሥርዓቶች የማዕድን ዘርፉ ለሌሎች ዘርፎች በተሰጠው ልክ ትኩረት ሳያገኝ መቆየቱን በማዕድን ሚኒስቴር የጂኦ ሳይንስና ምርምር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቶማስ ቱት ገልፀዋል፡፡

አሁን ላይ ግን መንግስት በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

በተለይም በወርቅ ማዕድን የሚታወቀው የጋምቤላ ክልል በስፋት ወርቅ በሚመረትባቸው አኝዋክ እና ማጃንግ ዞኖች ውስጥ ባሉ አራት ወረዳዎች ሐብቱን በተገቢው ጥቅም ላይ ለማዋል በሰፊው እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዘርፉ ለበርካቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ያነሱት ሚኒሰትር ዴኤታው ÷ በሥራ ሥምሪት በአራቱም ወረዳዎች በእኩል ደረጃ የመንቀሳቀስ ክፍተት እንዳለ አንስተዋል፡፡

እንደ ሀገር በርካታ የወርቅ ማዕድን እንደሚገኝባቸው የሚታወቁት የጋምቤላ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የኦሮሚያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እነደሆኑም ያነሱ ሲሆን ጥናት ቢደረግ በሌሎች ክልሎችም ማዕድናት ሊኖሩ እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡

በክልሎች ሐብቱን በአግባቡ ከመጠቀም አንፃር እና ለአካባቢው ነዋሪዎች ግንዛቤ ከመፍጠር አንጻር ውስንነቶች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው ወርቅ እየተመረተ ያለው አድካሚና አሰልቺ በሆነ ባሕላዊ መንገድ በመሆኑ ኅብረተሰቡ በዘርፉ ለመሰማራት ያለው ፍላጎት አነስተኛ ነውም ብለዋል፡፡

ወጣቶች ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ በአራቱም ክልሎች በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፕሮጀክት በመቅረፅ የአደረጃጀት እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን ዘርፉን መንግስት ብቻ ሳይሆን ሌሎች አካላትም ሊደግፉት ይገባልም ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version