Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ ምርቶች በቅናሽ ዋጋ የሚቀርቡበት የከተማ ግብርና አውደ ርዕይ ተከፈተ

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 2 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምርቶች በቅናሽ ዋጋ የሚቀርቡበት የከተማ ግብርና አውደ ርዕይና ባዛር በይፋ ተከፈተ፡፡

የአምራችነት ቀንን ምክንያት በማድረግ በፒያሳ አደባባይ ላይ የከተማ ግብርና አውደርዕይና ባዛር ተከፍቷል።

በምክትል ከንቲባና የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዣንጥራር አባይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ግብርና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሹጉጤን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በሀገር ወስጥ አምራቾች የተዘጋጁ ምርቶች በቅናሽ ዋጋ የሚቀርቡበት አውደ ርዕይ ተዘዋውረው በመመልከት አምራቾችን አበረታተዋል።

ምክትል ከንቲባው የከተማ ግብርና ከተጀመረ አጭር ግዜ ቢሆንም የሕዝቡን የፍጆታ ምርቶች ፍላጎትና ኑሮ ከማቃለል አንጻር እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻርም ለከተማ ግብርና አስፈላጊውን ግብአት በማቅረብና በመደገፍ ምርታማነቱን በማሳደግ የከተማዋን ነዋሪዎች ሕይወት በዘላቂነት ማቃለል ይገባል ብለዋል።

የከተማ ግብርናን በሚፈለገው ደረጃ በማሳደግና መሸጫ ሥፍራዎችን በከተማዋ ልዩ ልዩ አካባቢዎች በማበራከት የከተማዋን ነዋሪ እዚሁ በሚመረት የከተማ ግብርና ብቻ ተደራሽ ማድረግ መቻልን ጨምሮ በተጓዳኝ የአርሶ አደሮችን ሕይወት መቀየር ይቻላልም ነው ያሉት።

የከተማ ግብርናን መደገፍ የኑሮ ወድነትን ለማቃለል ካለው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባለፈ በሚፈለገው ደረጃ የገበያ ትስስር መፈጠሩ ደግሞ አርሶ አደሮችን ታሳቢ ያደረገ ዕድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው ማለታቸውን የከንቲባ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

በሁሉም ረገድ ምርትና ምርታማነትን እና አጠቃላይ ልማትን ለማስቀጠል የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የጥምር ጦር አባላት የኢትዮጵያን ቀጣይነት አጽንተው ለማስቀጠል የሕይወት መስዋዕት እየከፈሉ የሚገኙበት ወቅት በመሆኑ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ አስተማማኝ የኋላ ደጀን መሆን እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version