Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አሊባባ ግሩፕ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የትብብር ስምምነት አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2014፣ (ኤፍ ቢ ሲ) አሊባባ ግሩፕ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለስራ ፈጣሪዎች ስልጠና ለመስጠት የሚያስችላችውን ስምምነት አድርገዋል።

ስምምነቱ አሊባባ ግሩፕ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የቴክኖሎጂ ስራ ፈጣሪዎች ስልጠና ለመስጠት እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማህበር ደግሞ ሰልጣኞችን በመመልመል ውጤቱን ለመገምገም የሚያስችል ነው ተብሏል።

አሊባባ የሚሰጠው ስልጠና ለውሳኔ ሰጪ አካላት፣ ለስራ ፈጣሪዎች፣ ለቴክኖሎጂ ድርጅት ባለቤቶች፣ ለሰራተኞች እና ተማሪዎች ሲሆን የመጀመሪያው ዙር ስልጠና ለስራ ፈጣሪዎች የሚሰጥ እንደሚሆን ታውቋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ የዲጂታል ክህሎት ያለው ዜጋ ማፍራት ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ስልጠናም በዘርፉ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን በተለያየ መልኩ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን እውቀት የሚጨብጡበት ይሆናል ብለዋል።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማህበር ፕሬዚዳንት ፍቅር አንዳርጋቸው ከአሊባባ ግሩፕ ጋር የተደረገው የስልጠና ስምምነት ኢትዮጵያ የያዘችውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ለመደገፍ የራሱ አስተዎፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የአሊባባ ግሩፕ የዲጂታላይዜሽን ቢሮ ከፍተኛ አማካሪ ሳሚ ፋራድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኢ-ኮሜርስ የሎጂስቲክስ ማዕከል ለመሆን እየሰራች ያለውን ስራ አሊባባ ግሩፕ እንደሚደግፍ አውስተዋል።

አሊባባ ግሩፕ የሚሰጠው ስልጠና ስራ ፈጣሪዎች አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እና ድርጅቶቻቸውን እንዲያዘምኑ የሚያስችላቸው መሆኑንም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version